የሐጎሳ አጭር ታሪክ ባማርኛ

የወላጃችን የወ/ሮ ሐጎሳ ወልደጊዮርግስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ወ/ሮ ሐጎሳ ወልደጊዮርግስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደጊዮርግስ ደበሳይና ወ/ሮ ማና ሐየሎም በጥር 24 ቀን 1906 ዓ. ም. አራዕዋየን በተባለው መንደር በኢሮብ ወረዳ ተወለዱ፡፡ ክርስትና በልደታ ማርያም ቁመስና ቤተ ክርስቲያን በአባ ቪንሰንት ተነሱ፡፡ የክርስትና እናታቸው ደግሞ እናቴ ፍሥሐ ፍሡሕ ከአራዕዋየን  ነበሩ፡፡

ወ/ሮ ሐጎሳ ገና ጨቅላ ሕፃን እያሉ እናታቸው በሞት ከዚህ ዓለም ተለዩባቸው፡፡ በሕፃንነታቸው ባጣም ፈጣንና ብልህ ሴት ልጅ ስለ ነበሩ፣  አባታቸው አቶ ወልደጊዮርጊስ ምን ልትሆ ይሆን ብለው ብዙ ያስቡና ይጨነቁ ነበር፡፡

ከእናታቸው ሞት  በኋላ፡ አክስታቸው ወ/ሮ ለቱ ደበሳይና ባለቤታቸው አቶ ሐሊቦ ፃዕሩ ወስደዋት አሳደጉዋቸው፡፡ እነርሱ ከወለዱት ልጆቻቸው በላይም እየተንከባከቡ፣ በጥሩ አስተዳደግና ሥነ ሥርዓት አሳደጉዋቸው፡፡ በስምንት ወንድ ልጆች መካከል ሰለነበሩ፣ ተወዳጅነት ነበራቸው፡፡ በተለይ አቶ ሐሊቦ ፃዕሩ ከአክስታቸው በላይ ይንከባከቡዋቸው እንደ ነበር ይተርኩ ነበር፡፡ አክስታቸው ኃይልኛ ስለነበሩ፣ ሲቆጧቸው አትንኳት እያሉ ይከላከሉላቸው እንደ ነበር እራሳቸው ይተርኩ ነበር፡፡ ወ/ሮ ሐጎሳ ከአከስታቸው በላይም አቶ ሐሊቦን ይወዱ እንደነበርም ይናገሩ ነበር፡፡ በማርና ወተት አሳደጉዋቸው፡፡

ወይዘሮ ሐጎሳ ካደጉ በኋላ፣ ለተወሰነ ጊዜ ከአባታቸው አቶ ወልደጊዮርግስ ደበሳይ ጋር በዓደግራት፡ ጎልዓ በተባለው ቦታ፡ ተቀምጦው ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ወደ አክስታቸው ወደ አዎ ተመለሱ፡፡ ለአካለ መጠን በደረሱ ጊዜም፣ አቶ ሐሊቦ ፃዕሩና ወ/ሮ ሉቱ ካባታቸው ወልደጊዮርግስ ጋር በመማከር፣  ከአቶ ባረኪ ወልደጊዮርግስ ጋራ ትዳር እንዲመሠርቱ አደረጉ፡፡ በአዎ በሚገኘው በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስርቲያን በቆሞስ አባ ተክለሃይማኖት ኣማካይነት ቃልኪዳንን አሠሩ፡፡ ወ/ሮ ሐጎሳ የ5 ወንድ ልጆችና የ2 ሴት ልጆች፡ በጠቅላላ የ7 ልጆች እናት ነበሩ፡፡ ከነዚህም አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሕይወታቸው እያሉ በሞት ተለዩባቸው፡፡ ከቀሩት አራት ወንድ ልጆች፡ ሁለቱ ዓለማውያን ሲሆኑ፣ ሁለቱ  ደግሞ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ካህናት ናቸው፡፡ አንድ ሴት ድግሞ ባለ ትዳር ናት፡፡ በሕይወታቸው እያሉ እስከ ሦስት ወለዶ ድረስ የልጅ-ልጆቻቸውን ለማየት በቁ፡፡


የወይዘሮ ሐጎሳ ባህርይ
በማኅበረ ሰብ ውስጥ በጣም ተወዳጅና ባለ መልካም ጠባይና ባህርይ የነበራቸው ሲሆን፣ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅነትን ያሰቀሩ እናት ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ተወዳጅ የሆነ ተፈጠሮ በእግዚአብሔር የታደላቸው ትዕግሥተኛና የሰው ወዳጅ፡ የደሃ እናት ነበሩ፡፡ ካፋቸው መጥፎ ነገር የማይወጣ፣ በተፈጥሮ ብልህ የሆነ እውቀት የታደሉ፣ እነዲሁም  ኃይለኛና የተፈጥሮ ዕውቀትና ጥበብ የነበራቸው እናት ነበሩ፡፡

ስለ መንፈሳዊ ሕይወት 
ወይዘሮ ሐጎሳ በእውነት መንፈሳዊትና ቤተ ክርስቲያንን የሚወዱ፣ የምሥጢራትን አዘውታሪት ነበሩ፤ በተለይም ንስሐንና ቅዱስ ቁርባንን መቀበልንና ማዘውተርን ይወዱ ነበር፡፡ የመቁጠሪያ ጸሎትን ከመጠን በላይ ይወዱትና ያዘውትሩት ነበር፡፡ ሌሊት የመቁጠሪያ ጸሎት  በመድገም ላይ ያድሩ የነበሩ መንፈሳዊት ወላጅ ነበሩ፡፡

ስለ ሥራ ሙያቸው

እናቶችን ሕፃናትን ከሚያዋልዱ ታላቅ እናት-ሴቶች አንዲትዋም ነበሩ፡፡ በሴት ሞያ ተዋዳደሪ የሌላቸው ሞያተኛ ሴት ነበሩ ለማለትም ይቻላል፡፡ በምግብ አሠራር፣ የቤት ዕቃን አያያዝ፣ የቤት አስተዳደር ልዩ የተፈጥሮ ስጦታ ነበራቸው።

በትዳር ኑሮአቸው
ወ/ሮ ሐጎሳ በትዳራቸው ታመኝና በቃልኪዳናቸው የሚያምኑ እናት ነበሩ፡፡ የትዳር ባለቤታቸው፡ ወላጃችን አቶ ባራኪ ወልደጊዮርግስ በጣም ንጹህ ልብ ያለቸው፣ የታወቁ ራሳቸውን የሚችሉ፣ እንግዳና ወዳጅ ዘመድም ተቀባይ ስለነበሩ፣ ቤታቸው ሁልጊዜ የእንግዳ ቤት ነበር። በዚህ ምክንያትም፡ እናታችን በሥራ በጣም ይጎዱ ነበር ለማለት ይቻላል። በዚህም ላይ፡ ባለቤታቸው ማለት አባታችን አቶ ባራኪ ቁጡና ኃይለኛ ሰው ስለነበሩ፣ በከባድ-ሥራቸው ላይ የሚከብድ ሕይወትም ነበራቸው ለማለትም ይስችላል፡፡ ይሁን እንጂ፡ በመልካም ጠባያቸውና ትዕግሥታቸው የቤት አስተዳደራቸውም ችሎታ፣ ሁሉን ያሸንፉት ነበር፡፡ ባለቤታቸው ተቆጥው ሲመጡ ሲያዩ ልጆቻቸውን ከፊታቸው አዙረው በጓዳ እየደበቁ፣ ደብቀውም ምግብ እየሰጡ ሁሉ ነገር በልዝብ አንደበታቸውና ትዕግሥታቸው ሁሉን እያስተካከሉ ያሰተዳድሩት ነበር፡፡ 

ወ/ሮ ሐጎሳ ባለ ብዙ ሀብተ ጸጋ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ይኸን ሁሉ ለማስተዳደር ብዙ ልፋትና ድካም፣ በብዙ ውጣና ውረድም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚለፉ፣ ታተሪ ሠራተኛ ነበሩ፡፡ የወለዱት ልጆች በብዛት ወንዶች ስለ ነበሩ፣ በገጠር ኑሮ በጣም ይጎዱ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል፡ ውሃን ለመቅዳት ሲሄዱ፣ እንስራ በጀርባቸው፡ ልጅ በእቅፍ አድርገው፣ ዕንጨትን ለማምጣት ሲሄዱም፣ እንደሱ ለከብቶቻቸው መኖ ሲፈልጉ፣ እንደዚያ  እያሉ ንብረትን ሁሉ በጥበብ ለማሰተዳደር ይጥሩ ነበር፡፡ ባለ ብዙ ፍየልና ከብት ባለቤትም ነበሩ፤ እርሻም በአገሩ ደረጃ ጥሩ ምርት የሚያገኙበት፣ ማርና ወተት ቅቤም የመሳሰለ ቤታቸውን የማይለቅ፣  የሞቀ ቤት ነበራቸው፡፡ በሥራ ግን ከፍተኛ ልፋት የነበራቸው ወላጅ-ሴት ነበሩ፡፡ በገጠር እንደዛሬ ወፍጮ በየቦታው ተተክሎ ባልነበረበት ጊዜ፤ በባህላዊ ዲንጋይ ወፍጮ ሌሊት እህልን እየፈጩ እያደሩ፣ በነገታው ለስምንት ቤተሰብ እንግዳን ጨምሮ፣ ምግብን ማዘጋጀት፣ ከሌላው ሥራ ጋር ተጨምሮ፣ ከባድ ድካም እና ልፋት ያለው ሕይወት ነበራቸው፡፡ ቢሆንም ይኸንን ሁሉ በትዕግሥት ችለው፣ ለትዳራቸው ሲሉ በፍቅር በመሸከም፣ በደሰታ ይፈጽሙት ነበር፡፡ በመጨረሻም  ሁለተኛው ታላቅ ልጃቸውና የሚወዱዋቸው የትዳር  ባለቤታቸው፣ በአንድ ዓመት ልዩነት በሞት ስለተለዩባቸው፣ በታላቅ ሐዘን ላይ ወድቀው ነበር፡፡


ከዚያም በኋላ፡ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን እያስተማሩና እያስተዳደሩ እያሉ፣ የነበሩዋቸው 100 ፍየሎች፣ 16 ከብቶችና 6 አህዮች፣ በድንበር-ጥያቄ ምክንያት በተነሳው ግጭትና በወረራ ጊዜ፣ የሻዓቢያ ወታደሮች በሙሉ ወሰዱባቸው፡፡ ከዚያም በኋላ፣  የኖሩበትንና ልጆቻቸውን ሁሉ የወለዱባቸውን ሙቅና ጥሩ ቤታቸውን ጥለው፣ ተፋናቅለው ለስደት ተዳረጉ፡፡ ለከፍተኛ ችግርና መከራም ተጋለጡ፡፡ የሚወዱትን ቤታቸውንና ቋዋሚ ንብረታቸውን ጥለው፣ ከደውሃን ወደ አዎ ወደተባለው መንደር ወጡ፤ እዚያ በዘመድ ቤት ትንሽ ከቆዩ በኋላ፣ ወደ ዓዲግራት ሄዱ፡፡ እዚያ ከልጃቸው መምህር ፍጹም ባራኪ ጋር የተወሰነ አጭር ጊዜ ከቆዩ በኋላ፣ በልጆቻቸው ወደ መቀሌ እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ 

መቀሌ እንደገቡ ደግሞ፣ ከልጅ ልጆቻቸው ጋራ በኪራይ ቤት ውስጥ ተቀመጡ፡፡ አንድ ዓመት ቤትን በመከራየት ከተቀመጡ በኃላ፣ ልጆቻቸው ቦታ ገዝተውላቸው፣ ቤት ተሠርቶላቸው በቤታቸው ውስጥ ገቡ፡፡ እዚያ ለሁሉ ቤተሰብና ዘመድ መጠለያና ማደሪያ ሆነው፣ የልጅ ልጃቸውን እያስተማሩ ኖሩ፡፡ ከኤርትራና ኢትዮጵያ ህውከት በኋላም፣ ወደሚወዱት ቤታቸው ደውሃንና ማዶረ አልተመለሱም፡፡ 


 የ104 -ዓመት የልደታቸውን መግቢያ በዓላቸውን፡ በጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም.፡ ቤተሰብ በሙሉ በየአሉበት የምስጋና ቅዳሴን ቀድሶዉላቸው ዋሉ፡፡ በነበሩበት በመቀሌ ቁምስናም፣ የተከበሩ ቆሞስ አባ ጥዑም በርሄና ምክትል ቆሞስ አባ ሐጎስ የምስጋናን ቅዳሴ ቀድሶውላችው፣ አጅበው እያጫወቱዋቸው ዋሉ፡፡ በነገታው ምክትል ቆሞስ ቅዱስ ቁርባንን ይዘውላቸው መጥተው፣ ንስሐ ገብተው ቅዱስ ቁርባንን ተቀበሉ፡፡


ከዚያ ከ10 ቀኖች በኋላ፣ በየካቲት ወር ውስጥ አሞዋቸው፣ ልጃቸው አቶ ኃይሉ ባረኪ ከደውሃን፡ በየካቲት 14 ቀን፡ ታላቁ ልጃቸው አባ አብረሃ ባራኪ ደግሞ፡ ከአዲስ አበባ በየካቲት 15 ቀን፡ በስድስት ሰዓት ገብተው፣ ጸሎት አድርጎውላቸው፣ አንድ ሰዓት ከቆዩ በኋላ፣ በልጆቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ተከበው ሳሉ፣ በሰባት ሰዓት በሰላም አረፉ፡፡ የሚገርም ነገር ቢኖር፣ የአንድ ሰው ሥጋና ነብስ ሲለያዩ፣ ሌላ ጊዜ ስቃይና መገለባበጥ ወይም የሥቃይ ምልክቶች  በፊት አንድ ነገር እንኳን ያሳያል። ነብሰ ኄርት ወ/ሮ ሐጎሳ ግን ምንም ዓይነት አንድ የስቃይ ምልክት ሳያሳዩ፣ ለማንም ሳያስቸግሩ፣ ፊታቸው የሚስብ ብርሃን መልክ ለብሰው፣ ደምቀውና አምረው በሞት ከዚህ ዓለም ተለዩ፡፡ ዕረፍታቸው የቅዱሳን ዕረፍት ይመስል ነበር፡፡


በየካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በዓሊቴና በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ መጀመሪያ የክርስትና ጥምቀትን በተቀበሉበት ቤተ ክርስቲያን፣ በልጆቻቸውና ልጅ-ጆቻቸው፡ በብዙ ወዳጅና ዘመድ ታጅበውና ተሽኝተው  የአዳምን አፈር ለበሱ፡፡ 

የውድት እናታችን የነብሰ ኄርት ወለተማርያም (ሐጎሳ) ነብስን እገዚአብሔር  በምሕረቱና በቸርነቱ በመንግሥተ ሰማይ ይቀበልልን፡፡ አሜን!


 (በአባ አብርሃ ባራኪ ተዘጋጀ)


No comments:

Post a Comment